የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለጭነት አገልግሎት ተግባር በ22 የመንገደኛ አውሮፕላኖቹ ላይ የምህንድስና ማስተካከያ /conversion/ አደረገ።

ግንቦት 10 ቀን፣ 2012 ዓ.ም

እንደሚታወቀው የአለማችንን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ያስቆመው የኮሮና ቫይረስ (COVID-19) ከሌሎች ዘርፎች በተለየ ሁኔታ የአየር መንገድ ኢንዱስትሪውን ከ90 በመቶ በላይ እንዲቆም አድርጓል። በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የመንገደኛ በረራዎቹን በተመሳሳይ ሁኔታ ከ90 በመቶ በላይ እንዲቆሙ በመደረጋቸው የተነሳ የአየር መንገዱን ህልውና የሚፈታተንና በታሪኩ የመጀመሪያ ከሆነው አለም አቀፋዊ ቀውስ ለመውጣት ሙሉ በሙሉ የስራቴጂክ እቅድ ለውጥ በማድረግ የትኩረት አቅጣጫውን ወደ እቃ ጭነት ቢዝነስ በማዞር እየሰራ ነው። ከዚህም ጋር በተያያዘ በመላው አለም እየጨመረ ለመጣው የጭነት አገልግሎት ፍላጎት በነበሩት የጭነት ማመላለሻ አውሮፕላኖች አጠናክሮ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱ ይታወሳል። ይህንን አዲስ ስትራቴጂ በመጠቀም የጭነት ማጓጓዝ አቅሙን ለማሳደግ ተጨማሪ 22 የመንገደኛ አውሮፕላኖችን የጭነት አገልግሎት እንዲሰጡ በውስጥ አቅም የምህንድስና ማስተካኪያ (Conversion) ተደርጎባቸው በጭነት አገልግሎት ስራ ላይ ይገኛሉ።

አየር መንገዱ በመንገደኛ አውሮፕላኖቹ ውስጥ የሚገኙ መቀመጫዎችን ከቦታቸው በማንሳት ስፍራው ለጭነት አገልግሎት እንዲውል ያደረገው አለማቀፍ የአቪየሽንና የቴክኒክ ተቆጣጣሪ አካላት ያስቀመጧቸውን መስፈርቶች በመከተልና በማሟላት ነው። አየር መንገዱ የኮሮናን ቫይረስ ለመዋጋት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ህይወት አድን የሆኑ የህክምና ቁሳቁሶችን በመላው አፍሪካ በማጓጓዝ ላይ ይገኛል። የአገልግሎት ተልእኮውን በብቃት ለመወጣትም በመንገደኛ አውሮፕላን የእቃ ማስቀመጫ ቦታ፣ እንዲሁም የአውሮፕላኖቹ ወንበሮች ሳይነሱ ጭነት በመጫን አገልግሎቱን በማቀላጠፍ ላይ ይገኛል።

አቶ ተወልደ ገብረማርያም፣የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ የጭነት አገልግሎት ፍላጎት ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ መምጣቱን አስመልክተው፣"የመንገደኛ አውሮፕላኖቻችንን ለጭነት አገልግሎት እንዲውሉ በማጥናትና በማስተካከል የምህንድስና ስራ ላይ የተሳተፉትን የአየር መንገዳችን የአውሮፕላን ጥገና ክፍል /MRO/ ብቁ ባለሙያዎችን ከልብ አደንቃለሁ፣አመሰግናለሁ። ይህ ተግባር በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የበርካታ ደንበኞቻችንን ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችለንን የተሻለ አቅም ለመፍጠር ያስችለናል። በዓለማችን የሚገኙ ህዝቦች የተከሰተውን ወረርሽኝ ለመመከት የሚያስችላቸውን የህክምና ቁሳቁስም ሆነ ሌሎች የመሰረታዊ ፍሎጎት ቁሶች በእጅጉ የሚፈልጉበት ግዜ ላይ እንገኛለን። በዚህ ታሪካዊና አስቸጋሪ ወቅት ይህንን አለም አቀፍ ወረርሽኝ ለመዋጋት ዋነኛ ተዋንያን በመሆናችን ደስተኞች ነን። ከዚህም ጋር በተያያዘ አገልግሎታችንን አሁን ካለበት በላቀ ደረጃ ለማሳደግ የተለያዩ አማራጮችን በማጤን ላይ እንገኛለን።" ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፈታኝ በሆነው በዚህ ወቅት የዓለምን ማሀበረሰብ ለማገልገል ባደረገው ጥረት ህይወት አድን የሆኑ የህክምና መሳሪያዎችን በበርካታ መጠንና ፍጥነት ያጓጓዘ ሲሆን፣ በዚህም አጠቃላይ የአገልግሎት ብቃቱን በማስመስከሩ ምስጋናና አድናቆት እየተቸረው ይገኛል።

CorporateCommunication@ethiopianairlines.com

(251-1)517-89-07/656/165/913/529

www.ethiopianairlines.com

www.facebook.com/ethiopianairlines

www.twitter.com/flyethiopian